Sacred Texts  Bible  World Bible  Index  Previous  Next 

Amharic Bible: 3 John

1:1 ሽማግሌው በእውነት እኔ ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ።

1:2 ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ።

1:3 ወንድሞች መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና።

1:4 ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም።

1:5 ወዳጅ ሆይ፥ ምንም እንግዶች ቢሆኑ፥ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ፥ እነርሱም በማኅበር ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤

1:6 ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳ መልካም ታደርጋለህ፤

1:7 ከአሕዛብ አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጥተዋልና።

1:8 እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል።

1:9 ወደ ቤተ ክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም።

1:10 ስለዚህ፥ እኔ ብመጣ፥ በእኛ ላይ በክፉ ቃል እየለፈለፈ የሚያደርገውን ሥራውን አሳስባለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፥ ሊቀበሉአቸውም የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል።

1:11 ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል። በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው፤ ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም።

1:12 ለድሜጥሮስ ሁሉ ይመሰክሩለታል፥ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም ደግሞ እንመሰክርለታለን፥ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።

1:13 ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም፤

1:14 ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አፍ ለአፍም እንነጋገራለን። ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ወዳጆችን በየስማቸው እየጠራህ ሰላምታ አቅርብልኝ።


Next: Jude